Connect with us

Hi, what are you looking for?

News

የርዕዮት ዜናዎች፤ 15 – ጥር – 2016

አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈናቃዮችን ይቅርታ ጠየቁ

በትግራይ የሚካሄዱ ሰልፎች ቀጥለዋል
በዛሬው ቀን ጥር 15 2016 በመቐለ ከተማ በተደረገ ሰለማዊ ሰልፍ በመዲናዋ የተጠለሉ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ያመሩ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ጋር ተነጋግረዋል፡፡

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፤ አስተዳደሩ ቀድሞ መስራት የነበረበትን ስራ ባለመስራቱ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን ተናግረው ለዚህም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ከአሁን በኋላ ጥያቄዎቻቸውን በመመለስ ወደ ቀያቸው እንደሚመልሷቸው ቃል ገብተዋል፡በሁሉም ስራችን ላይ በየቀኑ ከተወካዮቻችሁ ጋር በመገናኘት አብረን አንሰራለን ያሉ ሲሆን በሽረ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ጋር ያደረጉት ውይይት በሁሉም አካባቢ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በፅንፈኞች ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንደሚቀጥሉ ተናገሩ

የአማራ ክልልን ወደለየለት ብጥብጥና ትርምስ ለማስገባት የዘረፋና የውንብድና ተግባር እየፈፀመ ነው ያሉትንና ፅንፈኛው ቡድን ብለው የጠሩት ኃይል ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥና የቀጣናው ኮማንድ
ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሀኑ በቀለ ተናገሩ።

የቀጣናውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከክልል ከዞንና ከከተማ አስተዳደሩ ኮማንድ ፖስት አባላት ጋር በተልዕኮ አፈፃፀም፣ በተገኙ ውጤቶችና በቀጣይ የዘመቻ ስምሪቶች ዙሪያ በጎንደር ከተማ ውይይት ተደርጓል።

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የቅንጅት ስራ በመስራት ዘራፊውን ቡድን ትርጉም ወደ ሌለው ደረጃ ማድረስና የተገኘውን ሰላም ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስና ህዝቡ ወደ ልማት እንዲመለስ ሰራዊቱ ሌት ተቀን ስኬታማ የዘመቻ ስምሪቶችን እያደረገ ነው፤ ፅንፈኛውን ከህብረተሰቡ የመነጠል ስራም እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ይህን ስኬት ለማስቀጠልም ከሠራዊቱ ጋር በቅንጅት የመስራት አቅጣጫውን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ በኦሮሚያ መልሶ ለተቋቋመው ሲኖዶስ ምላሽ ሰጠ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በትናንትናው ዕለት መመስረቱን በመግለጫ ላስታወቀው መንበረ ጴጥሮስ ሲኖዶስ ምላሽ ሰጥቷል።

የቤተክርስቲያንዋ የቋሚና ጊዜያዊ ፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ መልአከ ህይወት ቆሞስ ወልደየሱስ ሰይፉ፤ ለሲኖዶሱ መቋቋም አራት ኤጲስ ቆጳሳትን ተጠያቂ አድርገዋል።

ቤተክርስቲያን ዘረኛ አይደለችም ያሉት ቆሞሱ፤ ይህ ፖለቲካ ነው ሲሉ ከሰዋል። በጫካ ለአንድ አመት ቆይተው በቤተክርስቲያን ላይ ዘመቻ እየፈጸሙ ነው ብለዋል። ሹመቱና ሲኖዶሱም የተወገዘ እንደሆነ አባ ወልደኢየሱስ ተናግረዋል።

የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ታገተ

የጋምቤላ ክልል መንግሥት ሰኞ እለት ከላሬ ወረዳ ወደ ጋምቤላ ከተማ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት “የተወሰኑ ሰዎች” መቁሰላቸውን አስታውቋል። ጥቃቱ የተፈጸመው፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና አቦል ወረዳ መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

የክልሉ መንግሥት ጥቃት ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ በክልሉ ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ “ጽንፈኛ
ኃይሎች” መኖራቸውን ጠቅሷል። ጥቃቱን ተከትሎ፣ ባካባቢው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቋረጡን ተሰምቷል፡፡

በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የጠለፋ ድርጊቶች መስፋፋታቸውን ዘ ጋርዲያን ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል። አራት ሰዎችን ማነጋገሩን የጠቀሰው ዘገባው፣ ሰዎቹ የተጠለፉ ቤተሰቦቻቸውን ለማስለቀቅ ከ20 ሺህ 500 ሺህ ብር ለማስለቀቂያ መክፈላቸውን እንደነገሩት ገልጽዋል። መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ቢወነጅልም ቡድኑ ሰዎችን ጠልፌ ገንዘብ በመጠየቅ ድርጊት ተሠማርቼ አላውቅም በማለት ያስተባብላል።

በፀጥታ ችግር 52 የመንገድ ፕሮጀክቶች መቆማቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለ2016 በጀት ዓመት ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከጠየቀው ከ682 ሺህ ቶን በላይ ሲሚንቶ ማግኘት የተቻለው 95,610 ቶን ወይም 14 በመቶ ብቻ መሆኑን ተሰማ፡፡

ከትናንት በስቲያ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሪፖርት ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን ለግንባታ ግብዓትነት ከተጠየቀው ነዳጅ ውስጥ ማግኘት የተቻለው 39 በመቶ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤

ችግሩ በጣም ያውካል፣ በጣም ከባድ ነው፡፡ መንግሥት ለህዳሴው ግድብ በሚያቀርበው ሁኔታ እንዲያቀርብልን ጠየቅን፣ ያልወጣንበት ያልወረድንበት ሁኔታ የለም፡፡ አሁን ያለን ተስፋና እየጠበቅን ያለነው በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያስፈልገንን ምርት ለማግኝት ነው፡፡


ከ238 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉኝ ያለው አስተዳደሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች የግብዓት እጥረትን በሚመለከት ከሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር፣ ከማዕድን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የአቅርቦት ችግሩ ለመፍታት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁንም መቀጠሉንና አሳሳቢ መሆኑን በሪፖርቱ አብራርቷል።

አስተዳደሩ ከግብዓት እጥረት በተጨማሪ በመላ አገሪቱ ካሉት 25 የፕሮጀክት ቢሮዎች 48 በመቶ በፀጥታ ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውን፣ ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቧል፡፡በፀጥታ ችግር ምክንያት ከፕሮጀክት አስተዳደር ኃላፊዎች መካከል ታግተው መለቀቃቸውን፣ መንገድ ላይ በሽፍታ መዘረፋቸውን፣ በጉባ ድልድይ አራት መሐንዲስና ዘጠኝ ባለሙያዎች መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡

በየጊዜው የሕይወት መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው የተባለ ሲሆን በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ሠራተኞች በፕሮጀክት ተሽከርካሪ ብቻቸውን መሄድ ባለመቻላቸው፣ ከሕዝብ ጋር በቅጥቅጥ አውቶቡስ ወይም በሚኒባስ በመሄድ ፕሮጀክቶችን እየተከታተሉ ነው
ብለዋል፡፡

በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶች ብዛት 52 መሆናቸውንም ተገልጽዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊላድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየር እንዳትሞክር ሲሉ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አስጠነቀቁ

የሶማሊው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ ማህሙድ ከአልጀዚራ ጋር ባካሄዱት ቃለምልልስ  ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ደረስኩ ባለችው ስምምነት መሰረት የምታገኘውን የባህር ላይ ዳርቻ መሬት ለመጠቀም እና ማንኛውንም ንብረቷን ልታንቀሳቅስ የምትችለው
የሶማሊያ ግዛትን አቋርጣ በማለፍ ብቻ ነው ሲሉ ገልጸው ይህንንም እንድታደርግ አንፈቅድም ብለዋል።

እስካሁን ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ግዛት ምንም አይነት እንቅስቃሴ አላደረገችም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ካደረጉ ግን ያኔ የተለየ መልክ ያለው ችግር ይፈጠራል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የግብጽ ሚሊተሪ ወደ ሶማሊያ እንዲገባ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ከግብጽ መንግስት ጋር አልተወያየንም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን በአሁኑ ሰአት በእኛ እምነት የተፈጠረው ችግር በዚያ ደረጃ ላይ አይደለም፣ ነገር ግን ወደ ለየለት ሁኔታ እንዳይገባ ነው ኢትዮጵያን እያስጠነቀቅን ያለነው፣ አትሞክሩት እባካችሁ እያልናቸው ነው ብለዋል።

Support Reyot Media:

Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb

Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about

Follow us:

Twitter: @reyotmedia

Facebook: @ReyotMedia

Instagram: @reyot_media

TikTok: @reyotofficial

Threads: @reyot_media

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Trending

You May Also Like

Sticky Post

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትውልድ ይፈርድብናል አሉ በትናትናው እለት በተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተገኝተው ንግግር ያሰሙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመረቀው ሙዚየም አገርን ለሆነው ላልሆነውማናወጥ፤...

Sticky Post

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አመራሮች እና የህወሓት ከፍተኛ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ተገናኙ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል...

Sticky Post

ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሹም ሽር አደረጉ በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ የሶስት ሚኒስትሮች ሹመት ጸደቀ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በቅርቡ ከሥልጣን የተሰናበቱትን ምክትል ጠቅላይ...

Sticky Post

ምክር ቤቱ ይፋዊ ይቅርታ ለመጠየቅ መቐለ ገባ በ ሸኽ ሓጂ ሙሐመድ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ የልዑካን ቡድን...