በትግራይ የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎችን አስተናገዱ
የምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞኖች ተፈናቃዮች በዛሬው ዕለት ጥር 13፤ 2016 ዓ.ም በተለያዩ ከተሞች ሰልፍ የወጡ ሲሆን የተለያዩ አካላት ጥያቄያቸውን እንድያደመጡ ጠይቀዋል።
በሽረና ዓደዋ በተካሄዱት ሰልፎች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም በመድሃኒትና እርዳታ እጦት በየቀኑ እየሞቱ እንደሆኑ ተፈናቃዮች ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የፌደራል መንግስት የውጪ ኃይሎች የተቆጣጠሩት አካባቢ ለቀው እንዲወጡና የክልሉ ግዛት ተመልሶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የምዕራብ ትግራይ ህዝብ በቀስታ እንዲጸዳ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ተሰላፊዎች የፕሪቶሪያ ስምምነት በአፋጣኝ በሙሉነት እንዲተገበር አሳስበዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ልዑክ ወደ ትግራይ ለመጓዝ ማቀዱ ተሰማ
የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጥር 18 እና 19 ጉብኝት ለማድረግ ቀጠሮ እንደያዘ የምክር ቤቱ አጋር የሆነው የምርምር ተቋም “አማኒ አፍሪካ” በድረገጹ አስታውቋል።
የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ በትግራይ የመጀመሪያውን ጉብኝት ለማድረግ ያሰበው ባለፈው ዓመት የካቲት ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ለጉብኝቱ “ተባባሪ ባለመሆኑ” ጉብኝቱ ሳይሳካ እንደቀረ “አማኒ” አስታውሷል።
ምክር ቤቱ በጉብኝቱ፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ሲቪል ማህበራትና በመቐለ ከተጠለሉ ተፈናቃዮች ጋር በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበርና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ይነጋገራል ተብሏል። በተያዘው ወር የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ጋና ናት።
ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ዛተች
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ በሶማሊያ ላይ ምንም አይነት ስጋት እንዲኖር እንደማይፈቅዱ እሁድ እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሲሲ “ማንም ሶማሊያን እንዲያስፈራራም ሆነ ደህንነቷን አደጋ ላይ እንዲጥል አንፈቅድም” ብለዋል።
ሲሲ አክለው “ግብፅን አትፈታተኑ፣ ወይም ወንድሞቿን አታስፈራሩ፣ በተለይ ደግሞ ጣልቃ እንድንገባ ከጠየቁ” ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።
ፕሬዝዳንቱ፣ ሱማሊያ የዓረብ ሊግ አባል በመሆኗ ሁሉም የሊጉ አባላት ከጥቃት ይጠብቋታል ብለዋል። “ወንድሞቻችን በተለይ ጣልቃ እንድንገባ ከጠየቁን ባትፈትኑን ይሻላል” ያሉት ሲሲ፣ አንድን መሬት ለመቆጣጠር ማሰብ ማንም ሊቀበለው እንደማይችል
ለኢትዮጵያ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በቤንሻንጉል የሚገኙ ጹኑ ታማሚዎች ወደ አዲስ አበባ ሄደው መታከም አለመቻላቸው ተገለጸ
አሶሳ ከተማን ከአዲስ አበባ የሚያገናኙ መንገዶች በጸጥታ ችግር በመዘጋታቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታማሚዎች ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ሆስፒታሎች ለመጓዝ እንደተቸገሩ ከሆስፒታሉ መስማቱን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።
በዚሁ ሳቢያ አዲስ አበባ ሂደው ከፍተኛ ሕክምና እንዲያገኙ ከሐኪሞች ወረቀት የሚጻፍላቸው ታማሚዎች ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን የሆስፒታሉ አስተዳደር መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል።
ሆስፒታሉ፣ ከፍተኛ የመድሃኒት እጥረት እንዳለበትና ባሁኑ ወቅት ከጤና ሚንስቴር መድሃኒት የሚያገኘው በአየር ትራንስፖርት ብቻ እንደሆነ መግለጹን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።
ትምህርት ሚኒስቴር የእንግሊዘኛ ትምህርትን አስቀረ
ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ ዓመት ጀምሮ “ስፖክን ኢንግሊሽ” እና “ኢንግሊሽ ሊትሬቸር” ከ“ኬጂ” ተማሪዎች የትምህርት ዓይነቶች መውጣቱን ተሰማ።
በአራት ዓመታቸው “ነርሰሪ” የሚገቡት ህጻናት፣ በስድስት ዓመታቸው ከ“ዩ ኬጂ” ሲመረቁ የሚያውቁት ብቸኛ የፊደል ገበታ የአከባቢው የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚጠቀምበትን ብቻ ይሆናል።
የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ህግ በማይከተሉ ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ ይህ የሚኒስቴሩ ውሳኔ በወላጆች ላይ ተቃውሞ ያጋጠመው ሲሆን ተማሪዎቹ አቅማቸውን እንዳያሳድጉ ያደርጋል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media