ምክር ቤቱ ይፋዊ ይቅርታ ለመጠየቅ መቐለ ገባ
በ ሸኽ ሓጂ ሙሐመድ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ የልዑካን ቡድን ባለፉት ዓመታት ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ጋር ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ለማስቀጠል በተደረሰው መግባባት መሰረት በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ እና ድጋፍ ለማድረግ ዛሬ መቐለ ገባ።
የልዑካን ቡድኑ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አመራሮች፤ በትግራይ እስልምና ጉዳይ አመራሮች እንዲሁም በመቐለ ሙስሊም ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸኽ አደም ዓብደልቃድር ባሰሙት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጦርነቱን ባለመቃወሙ ይቅርታ መጠየቁን ተከትሎ የሰላም ስምምነቱ እንዲጎለብት እና የተቸገረውን ለመካስ ተባብረን ለመስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሸኽ ሓጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የእስልምና መግቢያ የነጃሺ መገኛ የሆነችውን ትግራይ በጦርነቱ የደረሰባትን ውድመት ዳግም ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ያለፈውን ጊዜ በሚያካክስ መልኩ ለመስራት ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከትግራይ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ለማድረግ፥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን መጠለያ ጣቢያዎችን ለመጎበኝት እና በጦርነቱ እና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለመለገስ እንዳቀደ ድምጺ ወያነ ዘግቧል።
ኢሰመጉ በጎጃም ከ80 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው አረጋገጠ
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል በነበረ ግጭት ከ80 (ሰማንያ) በላይ የሆኑ በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ከግድያው በተጨማሪ የአካል ጉዳት፣ ድበደባ፣ ማስፈራራትና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል ብሏል።
ለግድያው ዋነኛ ምክንያት በግጭቱ ወቅት የነበረው ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መሆኑን የጠቆመው ኢሰመጉ በተጨማሪም ቤት ለቤት በመዘዋወር ግድያ መፈጸሙን ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን ጠቁሟል።
ከጥር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሟቾች አስክሬን በመርዓዊ ከተማ ማሪያም ቤተክርስቲያን በጅምላ ቀብር መፈጸሙን እና በከተማዋ የተፈጸመውን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪ አካባቢውን ለቆ እየወጣ ሆኑን ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል።
የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በአካል በመገኘት ምርመራ በማድረግ ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመላክቶ በክልሉ በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ አካላት በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያ ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል።
40 በመቶ የአፋር ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ እንደሚፈልግ ተነገረ
የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት እስከ ስድስት መቶ ሺህ ያህሉ የክልሉ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት ለችግር መዳረጉን ባለፉት ሦስት ሳምንታት በስድስት ዞንኖች ውስጥ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ላይ በተከናወነ የድርቅ ዳሰሳ ጥናት መለየቱን ለዶቼ ቬለ አስታውቋል።
በተደጋጋሚ እና በተደራራቢ በተስተዋሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ከሁለት ሚሊዮኑ የአፋር ሕዝብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው በድርቅ ምክንያት ቀጥተኛ የጉዳት ሰለባ መሆኑን የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ተናግረዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ በተለይ በሰሜናዊ ዞን እና በዞን አራት ውስጥ መሠረታዊ አገልግሎቶች በጦርነት የተቋረጡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ድርቅ ተዳምሮ የሕዝቡን አኗኗር ለፈተና መዳረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ የሚገዙት የኃይል ፍላጎታቸው መቀነሱን ተሰማ
ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 66 ሚሊዮን 274 ሺ 260 ዶላር ለማግኘት አቅዳ 47 ሚሊዮን 514ሺ ዶላር ብቻ ማግኘቷን አስታውቃለች።
ለጎረቤት ሀገራት ከሚቀርብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አፈጻጸም ተቋሙ ባቀደው ልክ ላለመሳካቱ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የገለጹት የኤሌክትሪክ ኃይል የሽያጭና ገቢዎች አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሚኒሊክ ጌታሁን ናቸው። የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚላክላቸው ጎረቤት ሀገር መካከል አንዷ የሆነችው ሱዳን ባለባት የጸጥ ችግር ሳቢያ የተላለፈላትን ኃይል ክፍያ በአግባቡና በወቅቱ እየከፈለች አለመሆኑ አንዱ ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ጅቡቲና ኬንያም ይወስዳሉ ተብሎ ከታሰበው የኃይል መጠን ፍላጎታቸው የቀነሰ መሆኑን ኃላፊው የገለጹ ሲሆን ይህም በተወሰነ ተጽእኖ ማሳደሩና የግማሽ አመቱ ክንውን ዝቅ እንዲል ማድረጉን አስታውቀዋል።
የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ ገበሬዎችን በማፈንና በከብቶች ዘረፋ ተከሰሱ
የኤርትራ ወታደሮች፣ ከትግራይ ክልል ጋራ አዋሳኝ በሆኑ የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን እያፈኑና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶችን እየዘረፉ እንደሆነ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ተመለከትሁት ያለውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የኢትዮጵያ ጤና ቡድን አባላት፣ በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ላይ ባደረጉት ግምገማ ላይ ተመሥርቶ ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ሪፖርት፣ በኤርትራ ኃይሎች የተፈጸሙ በርካታ አፈናዎችንና የከብት ዝርፊያዎችን መመዝገቡን፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ገልጿል።
የዜና ተቋሙ ሪፖርቱን ያገኘው፣ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ ከጠየቀ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሥልጣን እንደሆነም አመልክቷል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በሰጡት ምላሽ፣ “ሐሰት ነው” ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media