በኦሮሚያ ክልል ከአስር በላይ የመንግስት ኃይሎች በታጣቂዎች ተገደሉ
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ታጣቂዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት ሰዎችን ማቁሰላቸው ተነገረ፡፡
በወረዳው ኤርጋንሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ትናንት በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት የክልሉ መንግሥት የሚሊሺያ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን ጥቃቱ የደረሰው ሸኔ ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈፀሙት በአካባቢው ሰፍሮ ነበረ ያሉት የአገር መከላከያ ሠራዊት ቀበሌውን ለቆ ከወጣ ከቀናት በኋላ ነው ፡፡
በጥቃቱ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እስከአሁን ያሉት
ነገር የለም።
ሶስት ኤጲስ ቆጶሳት መታሰራቸው ተሰማ
“የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስትያን መንበረ ጴጥሮስ” ሲሉ የሰየሙትን ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ይፋ ካደረጉ የሃይማኖት አባቶች መካከል ሦስቱ ትላንት፤ ማክሰኞ መታሠራቸውን የእንቅስቃሴው አስተባባሪዎች ገልፀዋል።
አቡኖቹ የታሠሩት መግለጫውን ከሰጡ በኋላ ሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኘው ቢሯቸው ውስጥ እንዳሉ መሆኑን ከ“መንበር” ምሥረታው አስተባባሪዎች አንዱ መሆናቸውን ለቪኦኤ የተናገሩት ዲያቆን አክሊሉ ዓለሙ ገልፀዋል።
የፌደራል መንግስት ለትግራይ ተፈናቃዮች በቢልዮኖች ድጋፍ አድርግያለሁ አለ
በዚህ ሳምንት በትግራይ የተለያዩ ከተሞች በተደረጉ ሰልፎች ተፈናቃዮች ከአንድ አመት በላይ እርዳታ አለማግኘታቸው እና እየተራቡና በየቀኑ እየሞቱ መሆኑን እየገለጹ ባለበት ሁኔታ የፌደራሉ መንግሥት በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ አርዳታ አድርጊያለሁ አለ።
በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ መንግስት በበጀት አመቱ መጀመሪያ ስድስት ወራት መንግስት ከራሱ ካዝና 11 ቢሊየን ወጪ በማድረግ፤ ከለጋሽ ደርጅቶች ደግሞ 4 ቢሊየን በማሰባሰብ የ15 ቢሊየን ብር የምግብ እርዳታ ለተጎጂዎች አከፋፊያለሁ ሲል አስተባብሏል።
የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ከ9 ሚሊየን በላይ ተረጂዎች በቀጣይ ሁለት ወራት ድጋፍ ለማዳረስ እየሰራ መሆኑንም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ተናግሯል፡፡
ኢዜማ በአማራና ኦሮሚያ ያሉት ተፋላሚ ኃይሎችን ከሰሰ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ከዓይን እማኞች ሰበሰብሁት ያለውን መረጃ ጠቅሶ እንደገለፀው በድሮን የሚደረጉ የአየር ጥቃቶች ንፁሃን በሚኖርባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው። ኢዜማ ይህን ይፋ ያደረገው ዛሬ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ፓርቲው በመግለጫው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በሚደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎች ንፁሃን ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል። በተጨማሪም ፓርቲው በመግለጫው መንግስትን ብቻ ሳይሆን በተፃራሪው ቆመው የሚፋለሙትን ታጣቂዎችም ከተሞችን እንቆጣጠራለን በሚል የሚያደርጉት የከተማ ውስጥ ውግያ በሰው ሕይወትና ሀብት
ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ሲል ከሷል።
ፓርቲው በዚሁ በመግለጫው ቢደረጉ ያላቸውን ወደ ስምንት ገደማ ምክረሃሳቦች ዘርዝሯል።
ኤርትራ የጀርመን አውሮፕላን አገደች
የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌናሌና ቤርቦክ ወደ ጂቡቲ ለሚያደርጉት ጉብኝት በኤርትራ የአየር ክልል በኩል ለማለፍ የሚያስችል ፈቃድ ባለማግኘታቸው ወደ ሳዑዲ ለማቅናት መገደዳቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ለሶስት ቀናት በሶስት የአፍሪካ አገራት ሊያደርጉት በአቀዱት ጉብኝት በቀዳሚነት ወደ ጅቡቲ አቅንተው በሱዳን ውስጥ ስላለው ጦርነት እና በቀይ ባሕር ላይ ስላጋጠመው የደኅንነት ችግር ለመወያየት አልመው ነበር።
ሚኒስትሯ ጉዟቸው ከተስተጓጎለ በኋላ ባወጡት መግለጫ የጉዞ አቅጣጫቸው መቀየሩ በአጠቃላይ በቀጠናው ላይ ያለው አለመረጋጋት ነጸብራቅ መሆኑን በማመልከት፣ ሱዳን እና የመን ውስጥ ያለው ግጭት የአየር ክልላቸውን ለመጠቀም አለማስቻሉን ገልጸዋል።
ቤርቦክ በምሥራቅ አፍሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት ከጂቡቲ በተጨማሪ ወደ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የመጓዝ ዕቅድ አላቸው።
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media