የኢሮብ ህዝብ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተባለ
በትግራይ ክልልና ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚኖረው የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሁለት በመከፈላቸው ማኅበረሰቡ ለድርቅ፣ ለስደትና ለተለያዩ በደሎች መጋለጡን ተናገሩ፡፡
መድህን ኣውዓላ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ አሁንም ድረስ ከብሔረሰቡ ስምንት ቀበሌዎች ውስጥ እንዳልገዳ፣ ወርዓትስ፣ ዓገረለኩማና ዳያዓሊቴና በተባሉ አራት ቀበሌዎች የኤርትራ ሠራዊት ይገኛል። ነዋሪዎቹ ኢሮብን በአዲግራት በኩል ከተቀሩት የትግራይ ክልል ከተሞች ጋር የሚያገናኘው መንገድ አገልግሎት እንደማይሰጥ ገልጸዋል።
የኢሮብ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ምስግና በበኩላቸው እንዳሉት፤
ወደ 60 በመቶ የሚሆነው የብሔረሰቡ ግዛትበኤርትራ ሠራዊት ሥር ነው። ሁለቱን ቀበሌዎች ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯቸው የሚገኝ ሲሆን፣ የተቀሩት ሁለቱ ውስጥ ደግሞ በከፊል ሰፍሮ ይገኛል።
አስተዳዳሪው ከአዲግራት ወደ ኢሮብ የሚወስደው መንገድ በኤርትራ ሠራዊት ከመውደሙም ባሻገር አሁንም በሠራዊቱ ተዘግቶ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በወረዳው ከባድ ድርቅና ረሃብ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን የምግብ ድጋፍ አቅርቦትም የሰውን ሕይወት ሊያተርፍ በሚችል ደረጃ አይደለም። በመሆኑም የምግብና የውሃ እጥረት በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተዘግቧል።
ከነዚህ ተዳራራቢ ችግሮች የተነሳ ከጦርነቱ በፊት 32 ሺሕ የነበረው የኢሮብ ብሔረሰብ እየተመናመነ እየጠፋ ነው ሲሉ ነዎሪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብር መሰብሰብ አልቻልኩም አለ
የአማራ ክልል በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 71 ቢሊዮን 650 ሚልዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ማሳካት የቻለው 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው ተባሏል። ይህም የእቅዱን 24.7 በመቶ መሆኑን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የዕቅድ አፈፃፀሙ ዝቅ እንዲልም ዋነኛ ምክንያቱ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ሃላፊው አቶ ፍቅረ ማርያም ደጀኔ የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈጻጸጸምን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ
አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሶማሊያን ህዝብ ይቅርታ ጠየቀ
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ፤ ሶማሊያን በሚመለከት ለአንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለምልልስ ላይ ሶማሊያ “የቅኝ ግዛት ውጤት” እንደሆነች እና በአገሪቱ ውስጥ ስላላው የፀጥታ ሁኔታ የተናገሩትን በማስተባበል ነው አገሪቱን ሕዝብ እና መንግሥት ይቅርታ ጠየቁ።
አምባሳደሩ በሶማሊያውያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰውን ይህንን ቃለምልልሳቸውን በተመለከተ በአጭር የጽሁፍ መልእክታቸው የተጠቀሟቸው “ቃላት የተሳሳቱ” እንደነበሩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ሙክታር ትላንት እሁድ ጥር 19/2016 ዓ.ም. ይቅርታ የጠየቁበት ቃለ መጠይቅ የተላለፈው በፋና ቴሌቪዥን ነበር።
የተመድ የጸጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሊወያይ ነው
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አባላት “በአፍሪካ ሰላም እና ደኅንነት” በሚለው አጀንዳ ላይ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ሁኔታ ለመፍታት ዛሬ ከሰአት በኋላ ዝግ ምክክር ያደርጋሉ።
በቤንሻንጉል ጉምዝ ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች መንግስት ካሳ እንዲከፍላቸው ተጠየቀ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በታጣቂዎች ንብረታቸው የወደመባቸው 291 ባለሀብቶች ያቀረቡት የካሳ ጥያቄ፣ የፌዴራል መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ መቅረቡ ተገለጸ፡፡
ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባለሀብቶች በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የወደሙባቸውን ንብረቶችና ሌሎች ጉዳዮች አስመልክቶ ክልሉ ለማጣራት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መላኩን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ሹሞ ተናግረዋል፡፡
የባለሀብቶችን ጉዳይ በተመለከተ ክልሉ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቢልክም፣ ኮሚሽኑ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ለተቋቋመ ኮሚቴ ማስረከቡን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media