Connect with us

Hi, what are you looking for?

News

የርዕዮት ዜናዎች፤ 22 – ጥር – 2016

ኢሰመጉ በትግራይ በረሀብ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሀብ እየሞቱ ነው አለ

በትግራይ የፌደራል መንግስት እና ጊዜያዊ አስተዳደሩ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ባለመቻላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ አሳወቀ፡፡

በትግራይ ክልል ያለው ረሀብ አሁንም ድረስ ተገቢ የሆነ መፍትሔ እና ምላሽ ባለማግኘቱ ምክንያት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ያለው የኢሰመጉ መግለጫ በዋናነት የአገር ውስጥ ተፈናቃይ የሆኑ ሴቶች፣ ጨቅላ ህጻናት፣ አጥቢ እናቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ከሟቾች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር መያዛቸውን ገልጿል።

ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት የሆኑ እንደ የአሜሪካ ኤጀንሲ ለዓለም አቀፍ ልማት (USAID) እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በትግራይ ክልል እና በአማራ ክልል ያቋረጡትን የምግብ እና የመድሀኒት ድጋፍ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያስጀምሩ ጠይቋል።

ዕንባ ጠባቂ መንግሥት በትግራይና አማራ ክልሎች ድርቅ አሊያም ረሃብ መከሰቱን በይፋ ብያኔ እንዲሰጥ ጠየቀ

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ የጉዳት መጠን የተመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ መንግሥት ድርቅ አሊያም ረሃብ መከሰቱን በይፋ ብያኔ እንዲሰጥ ጠይቋል።

የባለሞያዎች ቡድን ወደ ሁለቱ ክልሎች በመላክ ናሙና ወስዶ የችግሩን ስፋት እንዳጠና የገለጸው ተቋሙ፤ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የደረሰውን ጉዳት እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሁኔታ በመዳሰስ የአሰራር ክፍተቶችን ማግኘቱን አመልክቷል።

የተረጂዎችን ቁጥር መለየትን ጨምሮ በተዋረድ ያሉ የመንግሥት ተቋማት የተለያዩ አሃዞችን ማውጣታቸውን የጠቀሰው ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ በራሱ ያሰባሰበውን ቁጥር ይፋ አድርጓል። ይህ በመሆኑም በትክክል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ተገቢውን እርዳታ ማቅረብ እንደማይቻል ዋና ዕንባ ጠባቂው እንዳለ ኃይሌ ተናግረዋል።

ተጎጂዎች በአግባቡ ባልተለዩበት ሁኔታ በተገቢው መንገድ እርዳታ ማቅረብ አይቻልም። ለምሳሌ የፌደራል መንግሥቱ 2.2 ሚሊዮን እያለ፤ የክልሉ መስተዳደር ደግሞ 4.2 ሚሊዮን ናቸው ማለት የ2 ሚሊዮን ክፍተት አለ። ስለዚህ 2 ሚሊዮን በትክክልም እርዳታ
ማግኘት እየተገባቸው ላያገኙ ይችላሉ ማለት ነው። ሁለተኛ በትክክልም አሀዙ 2.2 ሚሊዮን ከሆነ ደግሞ 2 ሚሊዮን ሕዝብ በሌላ አካባቢ ለተቸገሩ መድረስ የሚገባው እርዳታ ለአንድ ክልል ሊሄድ ይችላል።

የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ለድርድርና ለውይይት በሩ ክፍት መሆኑን አስታወቀ

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ መንግስት  ከማንኛውም ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር  ልዩነቶችን በሰላምና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

ፓርቲያችንና መንግስታችን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጭምር ስብሰባ አካሂዷል፣ ውሳኔዎች አስቀምጠዋል፣ በየትኛውም ጊዜና ሰዓት ቢሆን ሰላማዊ  በሆነ መንገድ ለመወያየት ሀሳብ አለኝ ብሎ ለመደራደር፣ ለውይይት የሚመጣ ማንኛውም ሰላምን የመረጠ ሁሉ፣
ትጥቅና ነፍጥ አንግቦ ከመንቀሳቀስ ውጪ ሰላማዊ ለሆነ ውይይት ለመምጣት ለሚፈልግ ሁሉ ዛሬም ነገም፣ የመንግስት የሰላም በር ክፍት ነው የሚል አቋም ላይ ተደርሷል፣ የክልልም፣ የፌደራልም አቋም ይህ ነው፡፡

በአንፃሩ በምስራቅ ጎጃምና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን ውጊያዎች እንደነበሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ አባል ከአባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለቀቁ

የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አትንኩት መዝገቦ ከአባልነታቸው መልቀቃቸውን በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ አትንኩት መዝገቦ በትናንትናው ዕለት ጥር 21 2016 ለህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በጻፉት ደብዳቤ ከአባልነታቸው በራሳቸው ፍቃድ እንደለቀቁ ያሳያል፡፡

የትግራይ የግብርናና ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አትንኩት መዝገቦ የብኄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው የተሸሙ ሲሆኑ በዚህ ወቅትም በኮሚሽኑ እያገለገሉ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ ከአባልነታቸው ራሳቸዉን ያገለሉበት ምክንያት በደብዳቤው አላስቀመጡም፡፡

በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አልተከለከሉም ሲል ሚኒስቴሩ አስታወቀ

በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ አልተከለከለም ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ አቶ ዋሲሁን አባተ ገለጹ።

በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል እየተከናወነ ያለው ሥራ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ለማበረታታትና በነዳጅ የሚሠሩት ደግሞ በብዛት እንዳይገቡ ለመከላከል የኤክሳይስ ታክስ መሆኑን አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡

Support Reyot Media:

Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb

Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about

Follow us:

Twitter: @reyotmedia

Facebook: @ReyotMedia

Instagram: @reyot_media

TikTok: @reyotofficial

Threads: @reyot_media

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Trending

You May Also Like

Sticky Post

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ትውልድ ይፈርድብናል አሉ በትናትናው እለት በተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተገኝተው ንግግር ያሰሙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመረቀው ሙዚየም አገርን ለሆነው ላልሆነውማናወጥ፤...

Sticky Post

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አመራሮች እና የህወሓት ከፍተኛ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ተገናኙ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እና የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል...

Sticky Post

ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሹም ሽር አደረጉ በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ የሶስት ሚኒስትሮች ሹመት ጸደቀ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በቅርቡ ከሥልጣን የተሰናበቱትን ምክትል ጠቅላይ...

Sticky Post

ምክር ቤቱ ይፋዊ ይቅርታ ለመጠየቅ መቐለ ገባ በ ሸኽ ሓጂ ሙሐመድ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ የልዑካን ቡድን...