ህወሓት የአመራር ማስተካከያ ለማድረግ መስማማቱን አስታወቀ
ሕዳር 2 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 41 ቀናት እንደፈጀ በተነገረለት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር፣ የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ ሹሞች፣ የቀድሞ የፓርቲው አመራር እና ሌሎች የተሳተፉበት ልዩ ስብሰባ መጠናቀቁን ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ትናንት ማምሻውን ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ አስታውቋል።
መደረግ የነበረበት ስብሰባ ቢሆንም፥ ትግራይ በድርቅና ረሃብ ባለችበት ሁኔታ ለ41 ቀናት የዘለቀ ስብሰባ በመቀመጡ ይቅርታ የጠየቀው ህወሓት፥ “ከአሁን በኃላ ግን በሙሉ አቅማችን የህዝባችን ችግር በመፍታት ላይ እንጠመዳለን” ሲል ቃል ገብቷል።
በዚሁ ልዩ መድረኩ የተነሱ እና መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ብሎ 6 ነጥቦች ያስቀመጠው ሕወሓት፥ በስብሰባው ዓለምአቀፋዊ፣ ቀጠናዊ፣ ሀገራዊና ውስጣዊ ጉዳዮች ተነስተው ለትግራይ የሚኖረው ትርጉም በጥልቀት ተዳሰዋል ሲል አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በመድረኩ ህወሓት “የስትራተጂ አመራር ድክመት” እንዳለበት ተነስቶ መግባባት እንደተደረሰበት የገለፀ ሲሆን ይህም ለፀረ ዴሞክራሲ ባህርያት ማደግ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር መንገስ፣ ለቡድናዊነት እና ሌሎች ችግሮች እንደዳረጉት አምኗል።
ከዚህ በዘለለ የፕሪቶርያ ውል አፈፃፀም በሚመለከት ግምገማ ማካሄዱ፣ በውሉ መሰረት ተፈናቃዮች አለመመለሳቸው፣ የትግራይ ግዛት አለመመለሱ፣ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች የተጠያቂነት ጉዳይ ችላ መባሉ፣ ከፌደራል መንግስቱ ጋር ቀጣይ ፖለቲካዊ ድርድሮች አለመካሄዳቸው መነሳቱ ተገልጿል።
በስብሰባው በትግራይ በፓርቲ እና መንግስት መካከል ያለ መዘበራረቅ እንዲቀር፥ አሰራር እንዲበጅ መግባባት ላይ መደረሱ፣ ከግምገማና ነቀፌታ በኃላ በህወሓት ስትራቴጂካዊ አመራር ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ተሰብሳቢው መወሰኑ፣ በቀጣይ ወደ ፓርቲ ጉባኤ ለመግባት ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉንም መግለጫው አውስቷል።
በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአራት ወራት ተራዘመ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በአማራ ክልል ባሳለፍነው ነሐሴ ለስድስት ወራት የታወጀውን አስቸኳይ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሟል።
አሜሪካ ጨምሮ የአውሮፓ አገራትና ተቋማት አዋጁ እንዲነሳ እየጠየቁ የነበረ ቢሆንም መንግስት አሁንም በክልሉ ስጋት አንዳለው የሚያረጋግጠውን አዋጅ አራዝሟል፡፡
አዋጁ በሁለት ተቃውሞ በሶሰት ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንደተራዘመም ተገልጿል፡፡
መንግስት የአብን ሊቀመንበር የነበሩትን የምክር ቤት አባል በቁጥጥር ስር አዋለ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) የመጀመርያው ሊቀመንበር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አበል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ ትናንት ምሽት በፀጥታ አካላት ከቤታቸው ተይዘው መታሠራቸው ተገለፀ።
የፖለቲከኛው ቤተሰብ መሆናቸውን የገለፁ ሰው ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የምክር ቤት አባሉ ምሽት 3 ሰዓት ገደማ አዲስ አበባ ውስጥ ከመኖሪያ ቤታቸው አምስት በሚደርሱ የፀጥታ አካላት “በሕግ ትፈለጋለህ” በሚል ተይዘው መወሰዳቸውን አረጋግጠዋል።
አብን ከተመሠረተ ጀምሮ በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን እስካስረከቡበት ወቅት ድረስ የፓርቲው የመጀመርያው ሊቀ መንበር ሆነው ያገለገሉት ደሳለኝ ጫኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወከሉ ጥቂት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አንደኛው ናቸው።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ባለፉት ጥቂት ወራት ይደረጉ በነበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤዎች ላይ ሲሳተፉ አልታዩም። የምክር ቤት አባሉ ጥር 23 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ቤታቸው መበርበሩን እና በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታሥረው እንደሚገኙ የቤተሰባቸው አባል ተናግረዋል፡፡
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media