16 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል ተባለ
መንግሥት በመላው አገሪቱ 16 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት አጋጥሞታል ያለ ሲሆን ገሚሱ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት የገጠማቸው እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚሹ እንደሆነ ታውቋል።
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች እና መንደሮች ያለው የምግብ እጥረት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ እንደመጣ ከሥፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ እየወሰደ ያለው እርምጃ በቂ እንዳልሆነ ይነገራል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿን ትመክታለች አሉ
የኢትዮጵያን ሉዕላዊነት ለማስጠበቅና “የታሪካዊ ጠላቶቿን” ትንኮሳ ለመከላከል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ዝግጁ ነው ሲሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ማዕከል ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን የአንድነት ኮርስ እጩ መኮንኖችን ማስመረቁን ተከትሎ የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኝት በመንቀሳቀስ ላይ ባለችበት ወቅት የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶቿ መሰረተ ቢስ ክሶችን እያቀረቡ ነው ብለዋል።
ለዚህም የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ልክ እንደሁልጊዜው የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ዝግጁ ነው ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የአደንዛዥ እጽ ስርጭትን መቆጣጠር አልቻልኩም አለ
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአደንዛዥ እጽና መድሃኒቶች ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመከላከል ሥራዎች ሲሰሩ የቆዩ ቢሆኑም ከችግሩ ስፋትና ባህሪ አንጻር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ተገለጸ።
ችግሩን ለመፍታትም አደንዛዥ እጾችና መድሃኒቶች ወደ ተቋማቱ እንዳይገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር የቁጥጥር ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ መንስኤዎችን፣ ልምዶችንና መፍትሄዎችን መሠረት ያደረጉ የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ የተማሪ ሥልጠናዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዶ ናስር ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት በችግሩ አሳሳቢነት ልክ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅትና በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሜሪካ በአማራ ክልል የተጣለው አዋጅ መራዘም አሳስቦኛል አለች
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማስኛ በአማራ ክልል የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በኢምባሲው የፌስቡክ ገጽ ባወጡት አጭር መግለጫ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉትን ውስብስብ ችግሮች መፍቻው ብቸኛው መንገድ ንግግር
ነው ብለዋል።
Support Reyot Media:
Go Fund Me: https://gofund.me/afe7b8cb
Patreon: https://www.patreon.com/reyot/about
Follow us:
Twitter: @reyotmedia
Facebook: @ReyotMedia
Instagram: @reyot_media
TikTok: @reyotofficial
Threads: @reyot_media